የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚያደርገውን በረራ በሳምንት ወደ አስር ጊዜያት ማሳደጉን አስታወቀ፡፡
በኤፕሪል 1973 ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በረራውን ቦይንግ 720-ቢ አውሮፕላን በመጠቀም በሳምንት ለሁለት ቀናት የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት አጅግ ዘመናዊ የሆኑ ኤርባስ 350 እና ቢ787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን በመጠቀም በሳምንት ለአስር ጊዜያት በቀጥታ በረራ እያካሄደ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በዚህም ከአስር ሺህ በላይ መንገደኞችን ወደ 60 አለም አቀፍ መዳረሻዎች እያጓጓዘ መሆኑን በዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ የአየር መንገዱ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
በለንደን ሂትሮ እና ማንቼስተር አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያደረግ የነበረውን በረራንም በማሳደግ በለንደን ጋትዊክ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሳምንት ለሶስት ቀናት ተጨማሪ በረራ ማድረግ መጀመሩን በዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ የአየር መንገዱ ጽ/ቤት ገልጿል፡፡
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በመንገደኞችና በካርጎ አገልግሎት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ስኬታማ እድሜን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በለንደን ጋትዊክ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሶስተኛውን ማረፊያ በይፋ አስመርቆ የበረራ አገልግሎት ጀምሯል፡፡
በለንደን ጋትዊክ አለምቀፍ በረራ በይፋ ሲጀመር የአየር መንገዱ የኮመርሻል ቺፍ ኢፊሰር አቶ ለማ ያዴቻ እንደተናገሩት ዩናይትድ ኪንግደም ላለፉት ሀምሳ አመታት ለኢትዮጰያ አየር መንገድ የመንገደኛና የካርጎ አገልግሎት ዋነኛ የገበያ መዳረሻ መሆኗን ገልጸው ፣ የሁለቱ ሀገራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት አሁን ለደረሰበት መልካም ደረጃ አየር መንገዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡
የአፍሪካና የዩናይትድ ኪንግደም ህዝብ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስክ ያለው ትስስር ይበልጥ እንዲዳብር አየር መንገዱ ህዝቦችን እና ንግዳቸውን በማጓጓዝ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግስት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በበኩላቸው አየር መንገዱ ለአፍሪካ፣ ለላቲንና ለአውሮፓ አህጉራት ሳይቀር አለም አሰቸጋሪ በሆነው የኮቪድ ወረረርሽኝ ሲጠቃና በርካታ ታላላቅ አየር መንገዶች ከስራ ውጪ ሲሆኑ ብቸኛውን የካርጎ አገልግሎት በማቅረብ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ መድሃኒት በማጓጓዝና የንግድ ልውውጡ እንዳይቋረጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጫወተው ሚና ቀላል አልነበረም ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራትን እርስ በርስ በማገናኘት ፣ የፓን አፍሪካ ስሜት እንዲዳብርም አስተዋጽኦው የሚታወቅ ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዊልች እንደተናገሩት የኢትየጵያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም መካከል ብቻ ሳይሆን በዩናይትድ ኪንግደምና በአፍሪካ መካከል ንግድ፣ ቱሪዝምና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲያድግ የተጫወተው ሚና ግንባር ቀደም ነው ብል ትክክለኛነቴን ይበልጥ ያረጋግጣል ብለዋል፡፡
እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ከአየር ብክለት ነጻ የሆነ ብቃትና ጥራት ያለው አገልግሎት መለያው ነው ያሉት አምባሳደር ዳረን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከዚህም በላይ የበረራ መስመሮችን እንዲጨምር የመንግስታቸው ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም እና በአየር ላንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጀር አቶ ሄኖክ ውብሸት በበኩላቸው ዩናይትድ ኪንግደም የአውሮፓ ማእከል እንደመሆኗ ለአየር መንገዱ ጠንካራና ጠቃሚ የገበያ መዳረሻነቷ የሚታመንበት ነው በማለት ፣ አሁን ያሉንን መዳረሻዎች ለማስፋት ከአየር መንገዱ ጋር አብረው በታማኝነት የዘለቁ ደንበኞቻችን ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በለንደን ጋትዊክ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዪጵያ አየር መንገድ ስራውን በይፋ ሲጀምር የዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባላት ፣ የንግዱ ማህበረሰብ ፣ የአየር መንገዱ የኢትዮጵያና የዩናይትድ ኪንግደም ሰራተኞች ፣ ጋዜጠኞች ፣የጉዞ ጸሃፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
Latest News
Browse allwe appreciate your help.