የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የልዑካን ቡድን የለንደን ቆይታ
በለንደን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ አስተባባሪነት ከዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ጋር በመቀናጀት እ.ኤ.አ ከዲሴምበር 13-15/2023 ባዘጋጀው የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም 11 አባላትን የያዘ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የልዑካን ቡድን በለንደን ከተማ ከሚገኙ 3 የብሪታንያ የንግድ ምክር ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥና የትብብር ግንኙነት ውይይት አደረጉ፡፡
ሶስቱ የንግድ ም/ቤቶች የብሪቲሽ ንግድ ም/ቤት፤ የብርቲሽ-ኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤትና የለንደን ንግድ ም/ቤት ናቸው። በሶስቱም መድረኮች የለንደን ኤምባሲ ም/ሚሲዮን መሪ አቶ በየነ ገ/መስቀል በአስተባባሪነትና ተወያይነት የተሳተፉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ደግሞ ፕሬዜዳንቱ አቶ መላኩ እዘዘው(ኢንጂነር) እና የም/ቤቱ ጸሃፊ አቶ ውቤ መንግስቱ ከሌሎች 9 የቦርድ አባላት ጋር ተሳትፈዋል። በዚህም ምክክር ኢትዮጵያ ስላላት የኢንቨስትመንትና የንግድ እድሎች ማስረዳት ከመቻሉም በላይ ይህንን እድል ለመጠቀም በሚቻልበት አግባብ ላይ ከንግድ ም/ቤቶቹ ጋር ምክከር ተደርጓል።
የብሪቲሽ የንግድ ዘርፍ ም/ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አን ሜሪ ማርቲን ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝምና ለንግድ ሥራዎች እምቅ አቅም ያላት ትልቅ አገር መሆኗን መገንዘብ መቻላቸውን ገልጸው የብሪታንያ የንግድ ምክር ቤት በዩናይት ኪንግደም የሚገኙ ሌሎች የንግድ ምክር ቤቶችን በማስተባበር በቀጣይ ትስስር ለመፍጠር የማመቻቸት ሥራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የብሪቲሽ – ኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር አርቲ ኃይሰኒ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ እምቅ አቅሞችን በሚገባ ለይተው እንደሚያውቋቸው ልምዳቸውን አካፍለዋል። አስከትለውም በሃገሪቱ በርካታ ለውጦች እንዳሉ ሆነው አንዳንድ ወሳኝ የሚታዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ ማነቆዎችን በጋራ ተቀናጅቶ መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመቀጠልም የለንደን የንግድ ምክር ቤት የዓለም አቀፍ ፓርትነርሺፕ ኃላፊ የሆኑት ማርታ ኮዝሎውሳካ የንግድ ምክር ቤታቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ አጋሮችና በዩናይት ኪንግደም ከሚገኙ የንግድ አጋሮች ጋር ተቀናጅተው መሥራት እንዲችሉ በንግድ ምክር ቤታቸው በኩል የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያና የዩናይትኪንግደም የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ተቋማዊ የትብብር ማእቀፍ በማዘጋጀት በቀጣይ አብሮ ለመስራት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንዳለባቸው፣ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሙም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በዩናይት ኪንግደም የንግድ ምክር ቤቶች በኩል ለኢትዮጰያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ በመድረስ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በቀጣይ ውይይቶችና ግኑኝነቶች ለመፈጸም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ከንግድ ም/ቤቶቹ ወይይቶች መጠናቀቅ በኋላ ሁሉም የኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤት አባላት በተገኙበት በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉብኝትና የማጠቃለያ ውይይት ተደርጎ በቀጣይ መሰራት ባለባቸው ስራዎችና ለዩኬ-አፍሪካ ኢንቨስትመንት ሰሚት ከወዲሁ መደረግ ስላለባቸው ዝግጅቶች ግንዛቤዎች ተይዘዋል።
Latest News
Browse allwe appreciate your help.