ኢትዮጵያ ያሏትን የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የካፒታል ገበያንና የሰነደ መዋእለ ነዋይ/ Securities Market/ እድሎችን ለንደን አየተካሄደ ባለው አለም አቀፍ የፋይናንስ ዘርፍ ጉባኤ ላይ አቀረበች፡፡
“ኢንቨስት አፍሪካ 2023” በሚል ለንደን ላይ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ አመታዊ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከኢንቨስትመንት አማራጮች በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የካፒታል ገበያንና የሰነደ መዋእለ ነዋይ /Securities Market/ እድሎችን ለዩናይትድ ኪንግደም እና ከተለያዩ ሀገሮች ለመጡ በፋይንናስ እና በባንክ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
10ኛ አመቱን በያዘውና ከመላው አለምና ከአፍሪካ በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ያካተተው ኢንቨስት አፍሪካ 2023 ጉባኤ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የመሩት የልኡክ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ሌሊሴ ነሜ ፣ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፣ የሰነደ መዋእለ ነዋይ እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የስራ ሃላፊዎች እና በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተገኝተዋል፡፡
የገንዘብ ሚንሰቴር ሚንስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በጉባኤው ላይ እንደተናገሩት በኮቪድ ፣ በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰት ድርቅን ተቋቁሞ የኢትየጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሶስት አመታት ከ 6.1 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አጠቃላይ አመታዊ ምርት ከ 126 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የተናገሩት ሚንስትር ዴኤታዋ የኢኮኖሚ እድገቱ የግሉን ዘርፍ በማካተት ይበልጥ ለማደግ የሚችልበት እድል ተከፍቷል ብለዋል፡፡
በተለይም ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ዋነኛ ትኩረቱ የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገትን ለማስዝገብ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ባለሃብቶች ክፍት ማድረግ ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ማነቆዎችን በመፍታት የተሳለጠ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ፣ በግብርና ፣ በማንፋክቸሪነግ፣ በቱሪዝም ፣ በማእድን እና በአይሲቲ ዘርፍ ሰፊ እድሎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ያልነበሩ በአሁኑ ወቅት ግን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ድርሻ 25 በመቶ ቀሪው ድርሻ ደግሞ በሀገር ውስጥና በውጪ ባለሃብቶች የሚሸፈንበት የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፍ፣ የሰነደ መዋእለ ነዋይ /Securities Market/ በቅርቡ ይፋ መደረጉን አስታውሰው እነዚህ እድሎች ከፍተኛ የፋይናንስ ባለሃብቶችን በመሳብ ረገድ ሰፊ ሚና እንዳላቸው በመግለጽ ባለሃብቱ በዚህ ዘርፍ እንዲሰማራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አያይዘውም የባንክ የህግና የቁጥጥር ስርአት ዝግጅቱ በመከናወኑ የባንክ ዘርፉን ለውጪ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ወ/ሮ ሊሊሴ ነሜ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የአንድ መስኮት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን፣ ባለሃብቱ በማንፋክቸሪንግ ፣ በግብርና ፣ በፋርማሲዩቲካል ፣ በቱሪዝም ፣ በአይሲቲ ፣ በማእድን ዘርፎቸ ላይ ቢሰማራ ትርፋማ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ህጎችና መመሪያዎች አለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ ለማድረግ በየወቅቱ ማሻሻያ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተው ኢትዮጵያ ካላት ምቹ የገበያ ፣ የጉልበት እና የጥሬ እቃ አቅርቦት አንጻር ተመራጭ እንደሆነች አስገንዝበዋል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግስት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በሌላ በኩል እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለአለም አቀፍ ገበያ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው ፣ መላው አለምን ሊያገናኝ የሚችል የአየር መንገድ እና የካርጎ አገልግሎት ያላት ፣ በቂና የሰለጠነ ወጣት የሰው ሃይል የታደለች ፣ሸማች የሆነ ማህበረሰብ ያላት መሆኗ ተመራጭነቷን ያጎላዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ የኢኮኖሚ ፣ የፋይናንስ፣ የቴሌኮም፣ የህግና የተቋማት ሪፎርሞችን በማካሄዷ የዩናይትድ ኪንግደም ታላላቅ ኩባኒያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት መቀጠላቸውን አስታውሰው ኤምባሲው ለባለሃብቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ከምንጊዜውም በላይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሰረድተዋል፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት መስሪያ ቤት የስራ ሃላፊዎችም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በጉባኤው ላይ ተናግረዋል፡፡
“ኢንቨስት አፍሪካ 2023” አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒሰቴር ሚንስትር ዴኤታ የመሩት ልኡክ ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በአማራጮች ላይ ከባለሃብቶች ጋር የቡድንና የግል ውይይታቸውን ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ፡፡
Latest News
Browse allwe appreciate your help.