ኢትዮጵያ አዳዲስና ጥንታዊ የቱሪስት ሀብቷን ለንደን ኤክሴል በሚገኘው አለም አቀፍ የጉዞ ገበያ ማእከል ላይ አስተዋወቀች፡፡
ከ 184 በላይ የአለም ሀገራት በተሳተፉበትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ፣ አለም አቀፍ እውቅና ያላቸው የተለያዩ ሀገራት አሰጎብኚዎች እና የጉዞ ጸሀፍት በተገኙበት በዚሁ አለም አቀፍ የጉዞ የገበያ ማእከል ኢትዮጵያ አለም አቀፍ እውቅና ካገኙ የቱሪስት ሀብቶቿ ጀምሮ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎቿን አስተዋውቃለች፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣የክልል ቱሪዝም ቢሮዎች ፣ ከ 16 በላይ የኢትዮጵያዊያን አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ዳያስፖራውና በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጋራ በተሳተፉበት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ መለያ የሆኑትን ቅርሶች ለጎብኚዎች እና አለም አቀፍ ለሆኑ አስጎብኚ ድርጅቶች በይፋ ቀርቧል፡፡
በኤክሴል አለም አቀፍ የገበያ ማእከል የኢትዮጵያ መድረክን በይፋ ያስጀመሩት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደተናገሩት መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የቱሪዝም ዘርፉ በመሆኑ ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ አውጥቷል ብለዋል፡፡
ለዘርፉ እድገት በተሰጠው ትኩረት ልክ ሀብቶችን ለአለም ለማስተዋወቅ ለንደን የሚገኘው ኤክሴል አለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ ማእከል ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን የተመለከቱና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተገኙበት የገበያ ማእከል ኢትዮጵያ በታሪክ ፣ በባህል ፣ በቅርስ ዘርፍ ያሉ ሀብቶቿን እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በክልሎች የተገነቡ ዘመናዊና ማራኪ መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ ሰፊ የስራ ድርሻችን ይሆናል ብለዋል፡፡
ከአፍሪካ ሀገሮች በኮቪድና በሰላም እጦት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው ቱሪዝም ፈጥኖ በማገገም ረገድ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗን በተመድ የአለም ቱሪዝም ድርጅት መረጃን ዋቢ በማድረግ የተናገሩት አምባሳደር ናሲሴ ሀብቶችን ይበልጥ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ገበያን ለመሳብ ምቹ እድል አሁንም አለ ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ለሁሉም ክልሎች እና የግሉ ዘርፍ ድጋፍና ስልጠና በመስጠት ማስተዋወቁን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አምባሳደር ናሲሴ ከአጫጭር ጉብኝቶች ባሻገር ቱሪስቶች ለቀናት ማቆየት የሚችሉ ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል ብለዋል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግስት ባለሙሉ ባለስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በአለም አቀፉ የገበያ ማእከል ከማቅረብና ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዘላቂ የሆነችውን ሀገራቸውን በበጎ የማስተዋወቅ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች በአዲስ አበባና በክልሎች በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ በመሆናቸው እነዚህን መዳረሻዎች ዳያስፖራው ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ለአለም ሀገሩን ማስተዋወቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡
በአለም የቱሪዝም ገበያ ማእከል የኢትዮጵያን መድረክ የዬርዳኖስ የቱሪዝም ሚንስትር እና ሌሎች አጅግ በርካታ እንግዶች እየጎበኙት ሲሆን እየተካሄደ ያለው ኤክሴል አለም አቀፍ የገበያ ማእከል የኢትዮጵያን ሀብቶች የማስተዋወቁ ተግባር ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ይቀጥላል፡፡
Latest News
Browse allwe appreciate your help.